በሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ሥር የሚተዳደረው “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የበይነመረብ ሚዲያ እሁድ፣ ሐምሌ 9፣ 2015 ለሰኞ አጥቢያ በቢሮው ውስጥ ያለ ካዝና ባልታወቁ አካላት ተሰብሮ፣ ንብረቱ ተዘርፏል። የሚዲያ ተቋሙ በሚሠራቸው ዘገባዎች ሳቢያ ተደጋጋሚ ጫናዎች እየደረሰበት ሲሆን፣ ይህ ዘረፋም የነዚህ ተደራራቢ ጫናዎች ተቀጥያ እንደሆነ ሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ያምናል። ትላንት እሁድ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ባልደረቦች እስከ ቀኑ 10፡00 ሰዓት በዜና ክፍሉ ውስጥ በሥራ ላይ ቆይተው፣ ቢሮውን ቆልፈው ከወጡ በኋላ፣ ዛሬ ጠዋት 1፡00 ሰዓት ገደማ ቀድመው የደረሱ ባልደረቦች የቢሮው በር እንደተቆለፈ ነገር ግን ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ የዜና ክፍሉ ንብረቶች የተቀመጡበት ካዝና በኃይል ተሰብሮ አግኝተውታል። በዘረፋው ካዝናው ውስጥ የነበሩ ሦስት አዳዲስ እና ዘመናዊ ዲጂታል ካሜራዎች፣ ሁለት ዙም ሌንሶች፣ ሌሎች አራት መደበኛ ሌንሶች፣ አራት ላፕቶፖች እና አንድ ስማርት የሞባይል ስልክ ተወስደዋል። ሐቅ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘረፋውን ቦሌ ክፍለ ከተማ ለሚገኘው ለአደይ አበባ ስታዲየም አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ያመለከተ ሲሆን፣ የጣቢያው ፖሊሶች በ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ቢሮ በመገኘት አሻራ አንስተው፣ የተወሰኑ ባልደረቦችን ቃል ተቀብለው መሄዳቸውን አስታውቋል፡፡
