656 ቤተ እምነቶች ሕገ ወጥ ናቸው ተብሏል
ሸገር ከተማን ዘመናዊና በፕላን ብቻ ግንባታ የሚካሄድባት ለማድረግ ሕግ ወጥ ግንባታዎችን የማፍረሱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሸመልስ አብዲሳ ገለጹ።
በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱህፋ የተመራ ልዑክ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሸመልስ አብዲሳ ጽ/ቤት በመገኘት፤ በሸገር ከተማ እየተከናወነ ባለው የመስጊድ ፈረሳ ጉዳይ ላይ ዉይይት ማድረጉን አስታውቋል።
ምክር ቤቱ ውይይቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ “የሸገር ከተማ አስተዳደር ”ከፕላን ዉጭ ተሠርተዋል“ ያላቸውን መስጂዶች ለማፍረስ ሲነሳ የሚመለከተውን የእስልምና ጉዳዮች አካላትን አለማወያየቱ እና በተደጋጋሚ ጊዜ የቀረበለትን የውይይት ጥያቄ አለመቀበሉ ቅሬታ መፍጠሩን በሙስሊም ተወካዮች በኩል በውይይቱ መነሳቱን ገልጿል፡፡
- See also: የግራንድ አፍሪካ ረን
ምክር ቤቱ ሕዝበ ሙስሊሙ የሸገር ከተማ መስጂድ ፈረሳ ጋር በተያየዘ በተፈጠሩት ሁኔታዎች እጅጉን መጎዳቱንና ማዘኑን በማብራራት፤ ተገቢውን ካሳና የሞራል ሕክምና እንደሚያስፈልገውም ጠቁሟል፡፡ የጸጥታ አካላት ሰላማዊ ሙስሊሞች ላይ በቀጥታ በመኮስ ሙስሊሞችን መግደላቸውና ማቁሰላቸው ተገቢ አለመሆኑን፤ እንዲሁም ንጹሃን ላይ በመተኮስ የገደሉና ያቆሰሉ አካላት በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑም በውይይቱ ላይ ጠይቀዋል።
በጉዳዩ ላይ ቅድሚያ ውይይት አለመደረጉ ስህተት መሆኑን ያነሱት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሸመልስ አብዲሳ፤ በሸገር ከተማ ዉስጥ ካሉት 800 የኹሉም እምነት ተቋማት መካከል 656 የሚሆኑት ከፕላን ዉጭ የተሠሩ በመሆናቸው ገልጸዋል፡፡
ሸገር ከተማ ከ20 እስ3 30 ሚሊዮን ነዋሪዎች ያላት ዘመናዊና በፕላን ብቻ ግንባታ የሚካድባት ከተማ ሆኖ ለመግንባት ሕግ ወጥ ግንባታን መከላከል፣ የተገነቡትን ማፍረስ እንደሚቀጥል የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ ለሂደቱ መሳካት የእምነት ተቋማት ተባባሪ እንዲሆኑ ጠይቀዋል፡፡
አዲስ የሚገነባውን የከተማ ፕላን “የማይመጥኑ” የተባሉ የቤተ እምነት ግንባታዎች በሕጋዊና ከተማውን በሚመጥኑ ተቋማት ለመተካት የሚደረገውን ሂደትም፤ የኦሮሚያ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አቅሙን በማጠናከር በዉይይት የእምነት ተቋማቱ ራሳቸው መፍረስ ያለባቸውን እንዲያፈሱ እንጂ ከአሁን በኋላ መንግሥት በራሱ ማፍረስ እንደሚያቆም አስታውቀዋል።
- See also: የህትመትና ማስታወቂያ ማሰልጠኛ አካዳሚ ተከፈተ
የእሰልምናን ጨምሮ የሌሎችም ቤተእምነቶችም ተቋማት በብዛት በሸገር ከተማ ፕላን ዉስጥ እንደሚካተቱ የጠቆሙት ፕሬዝዳንቱ፤ ለዚህም አስፈላጊውን የቤተእምነት መሥሪያ መሬቶችን በፕላኑ መሠረት ለምዕመኑ እንደሚሰጥና በቆርቆሮ ሳይሆን የከተማዋን ፕላን የሚመጥን በርካታ ዘመናዊ መስጊዶች በከተማው እንዲሰሩ እንደሚፈልጉም ተናግረዋል። አክለውም በሸገር ከተማ ለኢስላማዊ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ የሚሆን መሬት እንደሚሰጥም ተናግረዋል።
በሌላ በኩል፤ ካለፉት ኹለት ሳምንታት ጀምሮ እስከ ትናንት ድረስ የታሠሩትን ሙስሊሞችን መፈታትን አስመልክቶ ዛሬ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ የፌደራልና አዲስ አበባ ፖሊስ አመራሮች ጋር ዉይይት እንደሚደረግ ያስታወቀው ምክር ቤቱ፤ ያለምንም ልዩነት የታሠሩት ሙስሊሞች በጠቅላላው እንደሚፈቱ ያለውን እምነት በመግለጫው ገልጿል።
እንዲሁም፤ ባለፉት ኹለት ሳምንታት በአንዋር እና ኑር መስጂድ በሸገር ከተማ የፈረሱትን መስጂዶችን በመቃወም ላይ እያሉ የተገደሉ ሙስሊሞች በሸገር ከተማ በፈረሱት መስጂዶች ምትክ ከሚሠሩት መስጂዶች መካከል አንዱ የሸሒዶች መስጂድ ተብሎ እነርሱን ለማስታወስ እንደሚሰየም ያስታወቀው ምክር ቤቱ፤ በመስጂዱ ቅጥር ጊቢ ዉስጥም የሟቾችም ሥም ዝርዝር በጉልህ በሚታይ መልኩ ይጻፋል ብሏል።