ዳሸን ባንክና ኖቫ ኮኔክሽንስ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።ዳሸን ባንክና ኖቫ ኮኔክሽን…

Reading Time: 2 minutes
ዳሸን ባንክና ኖቫ ኮኔክሽንስ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።

ዳሸን ባንክና ኖቫ ኮኔክሽንስ በቀጣይ ሶስት ዓመታት ግራንድ አፍሪካ ረን እና ለተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ዕውቅና የሚሰጠው አፍሪካ ኢምፖክት አዋርድ ለማዘጋጀት የሚያስችል ስምምነት ዛሬ ጥር 1 ቀን 2017 ዓ.ም በዳሸን ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ተፈራርመዋል፡፡



ዳሸን ባንክን በመወከል ስምምነቱን የተፈራረሙት የባንኩ ቺፍ ስትራቴጂ ኦፊሰር አቶ ኤልያስ ሁሴን እንደተናገሩት ዳሸን ባንክ ኖቫ ኮኔክሽንስ የሚያዘጋጃቸው የነዚህ መርሃ-ግብሮች አጋር መሆኑን በሰሜን አሜሪካ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጋር ያለውን ትስስር ይበልጥ እንደሚያጠናክር አመልክተዋል፡፡



የኖቫ ኮኔክሽንስ መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ ጋሻው አበዛ (ዶ/ር) በበኩላቸው ዳሸን ባንክ ኖቫ ኮኔክሽንስ ባለፉት አራት ዓመታት ባዘጋጃቸው መርሃ-ግብሮች አጋር ሆኖ በመቆየቱና ይህን አጋርነቱንም በቀጣይ ሶስት ዓመታት ለማስቀጠል ፈቃደኛ በመሆኑ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ስምምነቱ ዳሸን ባንክ ከኖቫ ኮኔክሽንስ ጋር በመተባበር በቀጣይ ሶስት ዓመታት በአሜሪካ ዋሺንግተን ከተማ ግራንድ አፍሪካ ረን ስኬታማ በሆነ መልኩ ለማካሄድና ተፅዕኖ ፈጣሪ ለሆኑ ኢትዮጵያዊያን በየአመቱ ዕዉቅና ለመስጠት እንደሚያስችል ተመልክቷል፡፡



ስምምነቱ የተለያዩ የዳሸን ባንክ አገልግሎቶች በሰሜን አሜሪካ ለሚገኘው የዳያስፖራ ማህበረሰብ ዘንድ ይበልጥ ተደራሽ የሚሆኑበትን ዕድል እንደሚፈጥርና ዳሸን ባንክ ማኅበረሰቡ የሚሰባሰብባቸውን መርሃ-ግብሮች መደገፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያሳየበት መሆኑ ተገልፃል፡፡

ዳሸን ባንክና ኖቫ ኮኔክሽንስ ባለፈው መስከረም ወር በዋሺንግተን የተካሄደውን ግራንድ አፍሪካ ረን እና አፍሪካ ኢምፖክት አዋርድ መርሃ-ግብሮችን በጋራ ማዘጋጀታቸው ይታወሳል፡፡



ዳሸን ባንክ የዳያስፖራ የቁጠባ ሂሳብ፣ የዳያስፖራ ተንቀሳቃሽ ሂሳብ እና የዳያስፖራ የጊዜ ገደብ ተቀማጭ ሂሳብ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በውጭ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን የመኖሪያ ቤት መግዣ ብድር፣ የመኖሪያ ቤት ማደሻ ብድር፣ የግል መኪና መግዣ ብድር እንዲሁም ቋሚና ጊዜያዊ የቤት ዕቃዎች መግዣ ብድር አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል፡፡ የብድር አገልግሎቱ በተመቻቸው የመክፈያ አማራጮች ማለትም በውጭ አገር ገንዘብ ወይም በብር መክፈል የሚችሉበትና በተመቻቸው የመክፈያ ጊዜ አማራጮች መክፈል በሚችሉበት ሁኔታ በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በሃዋላ የቁጠባ ሂሳብ እና በውጭ አገር ገንዘብ የሚቀመጥ የቁጠባ ሂሳብ አማካኝነት በውጭ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከመደበኛው የወለድ ክፍያ እጥፍ የሚሆን ክፍያ የሚያስገኙ የቁጠባ አገልግሎቶች በመሰጠት ላይ ይገኛሉ፡፡

ከዌስተርን ዩኒየን፣ ዳሃብሺል፣ ኢዝረሚትና ሌሎች ከውጪ ገንዘብ ለመላክ ከሚያስችሉ አገልግሎቶች በተጨማሪ በቅርቡ የተጀመረው የካሽ ጎ አገልግሎት በተለያየ የአለም ክፍል ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ ኢትዮጵያ በቀላሉ ገንዘብ መላክ የሚያስችል አማራጭ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

በየአመቱ የጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሳምንት በሰሜን አሜሪካ የሚካሄደው ግራንድ አፍሪካ ረን እና አፍሪካ ኢምፖክት አዋርድ በርካታ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሚሳተፉበት የስፖርት ውድድር ከዓመት ዓመት ተወዳጅነቱ እየጨመረ የመጣ ሲሆን ከሩጫው ጀርባ ኢትዮጵያዊያን የሚገናኙበት እና ባህላቸውን ተሰባስበው የሚያከብሩበት እንዲሁም ለሌላው የማኅበረሰብ ክፍል የሚያስተዋውቁበት መድረክ አንደሆነ ተገልጿል።
171080cookie-checkዳሸን ባንክና ኖቫ ኮኔክሽንስ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።ዳሸን ባንክና ኖቫ ኮኔክሽን…

Share to...

Facebook
Telegram
WhatsApp
Twitter
Email
Print
ጌች ሐበሻ

ጌች ሐበሻ

ጌትነት ተመስገን (ጌች ሐበሻ) በማኀበራዊ ጉዳዮች እና ወቅታዊ መረጃዎችን በተለያዩ የማኀበራዊ ሚዲያዎች ላይ በመጻፍ ንቁ ተሳታፊ ነው።
ጌች ሐበሻ

ጌች ሐበሻ

ጌትነት ተመስገን (ጌች ሐበሻ) በማኀበራዊ ጉዳዮች እና ወቅታዊ መረጃዎችን በተለያዩ የማኀበራዊ ሚዲያዎች ላይ በመጻፍ ንቁ ተሳታፊ ነው።

Any Thought?

Be part of the Community! Comment, connect, spread some joy and let the fun begin!

YOU MAY ALSO LIKE