የተአምረ ማርያም መጽሐፍ በኦሮምኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ተመረቀ!በብፁዕ አቡነ ናትናኤልና በዲ/ን እንዳለው መለሰ …

Reading Time: < 1 minute
የተአምረ ማርያም መጽሐፍ በኦሮምኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ተመረቀ!

በብፁዕ አቡነ ናትናኤልና በዲ/ን እንዳለው መለሰ ወደ ኦሮምኛ የተተረጎመው ተአምረ ማርያም መጽሐፍ ሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ተመርቋል፡፡



መጽሐፉ በኦሮምኛ ፣ በግዕዝና በአማርኛ ቋንቋዎች ተዘጋጅቶና በማኅበረ ቅዱሳን የኤዲቶርያል አገልግሎት ተመርምሮ ለህትመት የበቃ ሲሆን አሳታሚና አከፋፋይ ማኅበረ ቅዱሳን መሆኑ ተገልጿል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በሰሜን አሜሪካ የሚኒሶታና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቤተ ክርስቲያን በቋንቋ ማገልገልንና መገልገልን ከሐዋርያት ተቀበላ እያስቀጠለች መሆኗን ገልጸው እኛም የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ኦርቶዶክሳውያንን መሠረት ያደረገውን መጽሐፍ  እንደ አቅማችን ተርጉመን ለህትመት አብቅተናል ብለዋል፡፡



ብዙ ከማውራት ትንሽ መሥራት የተሻለ ነው ያሉት ብፁዕነታቸው በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ይህንን አድርገናል፣ በቀጣይ ደግሞ የትርጉም ሥራዎችን ከዚህ በበለጠ ለመሥራት መጻሕፍትን እየመረጥንና እየተመካከርን ነው ብለዋል፡፡

እኛ ይህንን የትርጉም ሥራ ለመሥራት ያነሳሳን ምክንያት የቤተ ክርስትያንን ተደራሽነት በመረዳት ምእመናን በቋንቋቸው እንዲገለገሉ በማሰብ ነው ያሉት የመጽሐፉ ተርጓሚ ዲ/ን እንዳለው ቋንቋን ምክንያት በማድረግ በአጉል ትርክት የተጠቁ ሁሉ ሊማሩበት የሚገባ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡



የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ መ/ር ዋሲሁን በላይ  በበኩላቸው ማኅበረ ቅዱሳን መንፈሳዊ አገልግሎትን ለማስፋፋት መጻሕፍትን በተለያዩ ቋንቋዎች በመተርጎም ረገድ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን መሥራቱንና ወደፊትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

ፀሐይሽ አትጠልቅም መንፈሳዊ ማኅበር ለብፁዓን አባቶችና መጽሐፉ ለሚያስፈልጋቸው አብያተ ክርስቲያናት እንዲደርስ 100 መጻሕፍትን ወስደዋል።

በዕለቱ በሰሜን አሜሪካ የሚኒሶታና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ፣ ሌሎች ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ፣ የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ መ/ር ዋሲሁን በላይና የማኅበራት ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
147580cookie-checkየተአምረ ማርያም መጽሐፍ በኦሮምኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ተመረቀ!በብፁዕ አቡነ ናትናኤልና በዲ/ን እንዳለው መለሰ …

Share to...

Facebook
Telegram
WhatsApp
Twitter
Email
Print

Any Thought?

Be part of the Community! Comment, connect, spread some joy and let the fun begin!

YOU MAY ALSO LIKE