ጉድ ሰማሪታን ፑር ፋሚሊ ሰፖርት ድርጅት 128 በጎዳና ላይ የሚኖሩ ታዳጊዎችን የህይወት ክህሎት ስልጠና ላለፉት ሶስት ወራት ሰጥቶ ወደ የቤተሰቦቻቸው የሸኘ ሲሆን በምትኩ 320 የዕለት ምግባቸውን ማሟላት የማይችሉ በጎዳና እና በሴተኛ አዳሪነት ህይወት ውስጥ ያሉ ሴቶችን እና ህጻናትን የህይወት ክህሎት ስልጠና መስጠት መጀመሩን አበሰረ።
የድርጅቱ መስራችና ፕሬዝደንት ዶክተር መክሊት ፍሊጶስ የዚህ የድጋፍ ፕሮግራም አላማ በጎዳና ላይ እና የዕለት ምግባቸውን ማሟላት የማይችሉ ሴቶችን እና ህጻናትን በማገዝ ራሳቸውን እንዲችሉ እና ከአሰከፊው የጎዳና ላይ ህይወት እንዲላቀቁ ድርጅታቸው እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው ይህ መልካም ተግባርእንዲሳካ ጥረት ላደረጉ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ላልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ግለሰቦች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ጉድ ሰማሪታን ፑር ፋሚሊ ሰፖርት ግብረ ሰናይ ድርጅት ሴቶችን በኢኮኖሚና በክህሎት በማብቃት ላይ ያተኮረና በ2008 ዓ.ም የተቋቋመ ሀገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ኑራቸውን በጎዳና ላይ ላደረጉ ህጻናት እና ወጣቶች ፣ በሴተኛ አዳሪ ህይወት ለተጋለጡ ሴቶች፣ ለጉልበት ብዝበዛ ተጋላጭ የሆኑ ልጆችን፣ በተለያየ ችግር ምክንያት ትምህርት መማር ላልቻሉ ሕጻናትን በማስተማር የተለያዮ የሞያ ስልጠና በመስጠት እንዲሁም ከቤተሰብ ጋር የተለያዩትን ወደ ቤተሰብ በማቀላቀል በአነስተኛ እና ጥቃቅን የስራ ዘርፎች እንዲሰማሩ በማድረግ እየሰራ የሚገኝ መንግስታዊ ያልሆነ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው።