የዶ/ር እመቤት ልዩ ከፍተኛ የጥርስ ህክምና ክሊኒክ እህት ኩባንያ የሆነው ሜርስ ኮንሰልቲንግ እና ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኀበር ልዩ የግንባታ አገልግሎቶችን ለመስጠት እና ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ጉልህ አበርክቶ ለማበርከት የሚያስችለውን እና ሚናሮል ህንጻ 10ኛ ፎቅ ላይ የሚገኘውን ዘመናዊውን ቢሮ የተለያዩ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በይፋ በዛሬው እለት አስመርቆ ስራ መጀመሩን አበሰረ።
የሜርስ ኮንሰልቲንግ እና ኮንስትራክሽን መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሜሪያው ዓብይ ሰርፀወልድ በምረቃው መርሐግብር ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት ለዚህ ስኬት እንድበቃ ላደረጉ ተቋማት እና ግለሰቦች ምሰጋናቸውን አቅርበው ድርጅቱ “የተሻለ ሕይወት መፍጠር” ዋና ተልዕኮ እና ግብ በማድረግ የተመሠረተ ሲሆን ተቋሙ በተቻለ መጠን ደንበኞቹ የሚፈልጉትን በትክክል ሊወክሉ የሚችሉ የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ሜርስ ኮንስትራክሽን የህዝብ ስራዎች፣ አርክቴክቸር፣ መኖሪያ ቤት፣ የአካባቢ ምህንድስና እና አማካሪን ጨምሮ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ በሁሉም መስኮች ምርጡን ጥራት የሚከታተል ፣ ልምድ ያለው እና የፈጠራ ባለሙያዎች ቡድን ስብስብ መሆኑን በመድረኩ ላይ ተገልጿል።
መርሐግብሩ ላይ የተገኙት እና የእለቱ የክብር እንግዳ የአዲስ አበባ አስተዳደር ዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አያልነሽ ሀይለ ማርያም ባደረጉት ንግግር ወጣቶች ከኢንጂነር ሜሪያው ዓብይ በርካታ ቁምነገር መማር እንዳለባቸው ገልጸው በከተማ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ የኮንስትራክሽን ዘርፉ እያደገ መምጣቱን እና የሜርስ ኮንሰልቲንግ እና ኮንስትራክሽን ወደ ዘርፉ መቀላቀል ትልቅ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል።