ልክ በዛሬዋ እለት እ.ኤ.አ. ሰኔ 15 ፥1990ዓ.ም ታዋቂው ፀረ-አፓርታይድ መሪ ኔልሰን ማንዴላ በሶዌቶ ፣ ደቡብ አፍሪካ በተካሄደው ታላቅ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ለብዙ ደጋፊዎቻቸው ታሪካዊ ንግግር አደረጉ። ሰልፉ የተካሄደው ማንዴላ ከ27 አመታት በኋላ ከእስር የተፈቱበትን እለት ለማክበር እና በደቡብ አፍሪካ ለአስርተ አመታት ሲተገበር የቆየውን የዘር መለያየት ስርዓት (አፓርታይድ) እንዲያቆም ጥሪ ለማቅረብ ነበር።
” ዛሬ ከፊታችሁ የቆምኩት እንደ ነብይ አይደለም፤እንደ አንድ ትሁት አገልጋያችሁ እንጅ።ቀን ከለሊት መድከማችሁ እና የጀግና መስዋዕትነቶቻችሁ ዛሬ ከፊታችሁ በኩራት እንድቆም አብቅተውኛል።፡ስለዚህም ቀሪዎቹ የህይወቴ ዘመናት ለእናንተ የሚበረከቱ ይሆናሉ።በዚህች ነጻነትን በተጎናጸፍኩባት እለት ልባዊ እና የሞቀ ምስጋናዬን ያላሰለሰ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ ለመለቀቅ ላበቃኝ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ የትግል አጋሮቼ እና በእያንዳንዱ የዓለም ጫፍ ለሚገኙ ወዳጆቼ ማቅረብ እፈልጋለሁ።በሰላም፣በዴሞክራሲ እና በነጻነት ስም ሁላችሁንም ከልብ አመሰግናለሁ።”
የማንዴላ ንግግር ጠንካራ ጥሪ ነበር። የደቡብ አፍሪካ ህዝቦች ተባብረው አዲስ ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር እንዲረባረቡ እና እርቅና ይቅርታ እንደሚያስፈልግ በመግለጽ ሁሉም ደቡብ አፍሪካውያን ለወደፊት እኩልነት እና ፍትህ እንዲሰፍን ጥሪ አቅርበዋል።የማንዴላ ከእስር መፈታት እና ይህ ታላቅ የድጋፍ ሰልፍ ለለውጡ ለሚታገሉት አዲስ ተስፋን የፈጠረ በመሆኑ በፀረ አፓርታይድ ትግል ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣ ነበር። የአንድነት እና የእርቅ መልዕክቱ ህዝቡን ያስደመመ ሲሆን በመጨረሻም እ.ኤ.አ. በ1994 ማንዴላ የደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዝዳንት ሆነው እንዲመረጡ መንገዱን የጠረገ ነበር።
የሶዌቶ ሰልፍ በደቡብ አፍሪካ ታሪክ ውስጥ እጅግ የጎላ ታሪካዊ ክስተትነበር ። የማንዴላ ሃያል ንግግር ፣ ቃላቶቹ እና ተግባሮቹ የወደፊት ትውልዶች ወደ ተሻለ፣ ፍትሃዊ አለም እንዲሰሩ ማነሳሳታቸውን ቀጥለዋል።