ራስን ፍለጋ

Reading Time: < 1 minute

ቀን እንኳን ቀንን ይወልዳል። እባብ ነባር ቆዳውን ይገፋል። ወፎች በከፍታ ይበራሉ። ማረፊያ  ጎጆም አላቸው።

እኔ ግን ዛሬም እንደትላንቱ ትላንት ላይ ቀርቻለሁ። ጊዜ በብርሃን ፍጥነት ወደፊት ሲገሰግስ እኔ ተገላቢጦሽ ወደኋላ አፈገፍጋለሁ። በምን ልጓም ላስቁመው?

አዋላጅ ያጣች ምጧ የበረታ አዲስ እሷነቷን መታቀፍ የምትሻ ። በጠቀረሹ አሻራዎች ያደፈው የማንነት ቆዳዋን ገፋ አዲስ እና ልዩ  ትርጉም ያለው የማንነት ባለቤት የመሆን ጥማት።

እያዩ አለማስተዋል, እያደመጡ አለመገንዘብ,  እየዳሰሱ ትርጉም አለመስጠት, እየተራመዱ አለመድረስ, በሰው ተከቦ ሰውን አለመናፈቅ, እየደሙ አለመሳቅ,  ጤነኛ ሆኖ ሀኪም አለመሻት።በሰዎች ሚዛን አለመሰፈር።  በቁም እያሉ በድን አለመሆን።
ከምንም በላይ ሰው ሆኖ ሰው መሆንን አለመናፈቅ!

ካሰመሩልኝ የህይወት ጎዳና አፈንግጦ በእራስ ክንፍ በእራስ ከፍታ በእራስ መንገድ እየከነፉ ነፃ መውጣት!!

በጥልቁ በረቂቁ በማይደረስበት በእራስ ግዛት ተደላድሎ ማረፍ።

ቆይ ከሰው የተጣላን ይሸመግሉታል። ከእግዜሩ የተኳረፈን ይገስፁታል። ከእራሱ ጋር ውጊያ ለጀመረ  ኸረረረ የማን ያለህ ይሆን የሚባለው?

እራስ እንዳትሉኝ!!!….እራስማ  ለራሱ አሳንሶ ቆርሶ አያውቅም።  እንደውም  ምርኮኛ ለመሆኔ ዋነኛው ምክንያት እራሱ እራስ ተብዬ ይመስለኛል።

  ያዘነልኝ, የወደደኝ,የጠቀመኝ ይመስል …. ከእኔ ውጪ የሚያውቅልሽ የለም እያለ በምቾት ጀርባ እያባበለ እንዳልነቃ አድርጎኛል።

የእውነት እራስ ግን ማን ነው?  የቱ ነው? እኔን እኔ ያስባለኝ ምኔ ነው?

ብቻ ይህን እየጠየኩም ቢሆን … አሁንም የእራሴ አናጢ, የእራሴ ቀራፂ, የእራሴ ሰዓሊ, የእራሴ ሾፋሪ,  የእራሴ ሀኪም,  የእራሴ እራስ የመሆን ጥማት የየሰከንዱ የውስጥ ቅውሰቴ ሆኗል።

                               ✍️  መቅደላዊት አሰፋ
                                         01/10/15
54770cookie-checkራስን ፍለጋ

Share to...

Facebook
Telegram
WhatsApp
Twitter
Email
Print

Any Thought?

Be part of the Community! Comment, connect, spread some joy and let the fun begin!

YOU MAY ALSO LIKE