ዶ/ር ዲላኒ አባቷ የአእምሮ ህመም ነበረበት። የህክምና ተማሪ እያለች እሷ የምትማርበት ህክምና ትምህርት ቤት አባቷ አሞት ይገባል። አብረዋት የሚማሩ ተማሪዎች እንዳያይዋት ተደብቃ ነበር የምትጠይቀው።
የህክምና ትምህርቷን ጨርሳ የምርቃት ድግስ ስታዘጋጅ አባቷን አልጠራቸውም። “ሰዎች ሲያዩት ምን ይሉ ይሆን? እሱን ሲያዩት ስለ እኔስ ምን ያስባሉ?” በማለት ተሸማቅቃ ሳትጠራው አለፈ። ሰርጓ ላይ እንዲገኝ ልቧ ቢፈልግም አእምሮዋ ግን “ሰዎች ሲያዩት ምን ይላሉ?” በሚለው ሀሳብ ተይዞ ስለነበረ አሁንም አባቷን ሳትጠራ ሰርግ ሰረገች።
አንድ ቀን ስራ ላይ እያለች ስልክ ተደውሎ አባቷ እንዳረፈ ተነገራት። “ምን አገኘው?” ብላ ስትጠይቅ “ሰሞኑን ከፍተኛ ጭንቀት ላይ ነበረ። ዛሬ ከድልድይ ላይ ዘሎ ራሱን አጥፍቶ ነው።” ዶ/ር ዲላኒ ማመን አልቻለችም። ጊዜ ሲያልፍ ሀዘኑ ቀለል ቢልላትም ፀፀቱ ግን እረፍት ነሳት…
ዛሬ ዲላኒ ለጓደኞቿ ሳይሆን ለአለም በሙሉ ድምጿን ከፍ አድርጋ ስለ አባቷና በአጠቃላይ ስለ አእምሮ ህመም በየቦታው እየተዟዟረች ትናገራለች። ዝምታው እንዲሰበርና ሰዎች ቶሎ ወደህክምና እንዲሄዱ ትወተውታለች።
የአእምሮ ህሙማን ከቤተሰብ፣ ከማህበረሰብ እና ከተቋማት ማግለል ይደርስባቸዋል። ይሄ ደግሞ ሰዎች ቶሎ ወደ ህክምና እንዳይሄዱ ያደርጋል። ስለ አእምሮ ህመም ዝምታው ይብቃ!
©ዶ/ር ዮናስ ላቀው