Search
Search

እርግባይ ሀበሻ ትራቭል በይፋ ስራ መጀመሩን አበሰረ

Share Post ►

በቱሪዝም ባለሙያው በአቶ እርግባይ ወንድሙ የተመሠረተው እርግባይ ሀበሻ ትራቭል የምርቃት እና በይፋ ስራ ማስጀመሪያ መርሀግብር አስመልክቶ ባሳለፍነው እሁድ ሐምሌ 9 ቀን 2015ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በየካ ክፍለ ከተማ የሚገኙ ታሪካዊ እና ተፈጥራዊ ቅርሶችን ጉብኝት ተከናወነ።

የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በማጠናቀቅ በከተማ ጉብኝት ስራ በይፋ መጀመሩን ያበሰረው የእርግባይ ሀበሻ ትራቭል ዋና ስራ አስኪያጅ እና መስራች አቶ እርግባይ ወንድሙ በቀጣይ ከተለያዩ አጋር አካላት እና ተቋማት ጋር በቅንጅት በመስራት አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ታሪካዊ ፣ ተፈጥራዊ እና ሰው ሰራሽ የመስህብ ስፍራዎችን በማስጎብኘት በመነቃቃት ላይ ያለውን የቱሪዝም የስራ እንቅስቃሴ በማገዝ አይነተኛ ድርሻ እንደሚወጣ በተለይ ለየኔ ቫይብ የዝግጅት ክፍል አሳውቀዋል።

በጉብኝት መርሐግብር ላይ ከኮኮበ ጽብሃ ትምህርት ቤት ጀርባ ከደብረ እንቁ ልደታ ማርያም ቤተክርስቲያን አጠገብ ላይ የሚገኘውን የአዲስ አበባን የከተማዋን ገጽታ ከከፍታ ቦታ ላይ የሚያሳየውን ስፍራ ፣ ከ320 ዓ.ም በፊት ከአንድ አለት ተፈልፍሎ የታነጸው ዋሻ ሚካኤል እንዲሁም ከዋሻ ሚካኤል ጋር ተያያዥነት ያለው ጥንታዊው የየካ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የጉብኝቱ አካል
የነበረ ሲሆን በጉብኝት መርሐግብር ላይ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እና ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈውበቷል።

ከአዲስ አበባ በቅርብ እርቀት ላይ የሚገኘው እና በጥንት ስሙ ዋሻ ቅዱስ ሚካኤል በአሁን ደግሞ ዋሻ ደብረ መንክራት አቡነ ተክለሃይማኖት ወ ቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን በ320 በአብርሃ ወ አጽባሃ ዘመን እንደተፈለፈለ የደብሩ የስብከተ ወንጌል ኃላፊ ሊቀ ትጉሃን ይኸይስ ፈንቴ ለጎብኝዎች የገለጹ ሲሆን ስፍራው እንደ ላሊበላ ከአንድ ወጥ አለት ድንጋይ ላይ የተዋቀረ ፍልፍል ዋሻ የአዲስ አበባ የመጀመርያው ቤተክርስቲያን ፣ በመሬት ላይ አስገራሚው አስደናቂ የአፍሪካ ካርታ መገኛ ፣ ለህዝበ ክርስቲያኑ የተደበቀ የቅርብ እሩቅ ስፍራ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ቦታው በ1878 ዓ.ም የቤተክርስቲያኑ ግድግዳዎች ፈርሰው በመውደቃቸው አገልግሎት መስጠት እንዳቆመ የጽሁፍ ድርሳናት ላይ ተገልጾ ይገኛል ብለዋል።

ሊቀ ትጉሃን ይኸይስ ፈንቴ አያይዘው እንደገለጹት
በአካባቢው የሚኖሩ የእድሜ ባለጠጎች በጣሊያን ወረራ ወቅት በፋሺስት ጣሊያን በቦምብ በተመታ ወቅትም ተጨማሪ ጉዳት ከደረሰበት በኋላ አሁን የሚታየው የውቅር ቤተክርስቲያኑን ሁኔታ ይዞ እስካሁን ይገኛል ብለዋል። በተለይ ቅርሱን ለቀጣይ ትውልድ ተጠብቆ ለማስተላለፍ ቤተክርስቲያኗ የበኩላን ድርሻ እየተወጣች ቢሆንም ቅርሱን እንዳይጎዳ የሁሉም ድርሻ ወሳኝነት እንዳለው ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የጉብኝቱ አካል የነበረው ከዋሻ ሚካኤል ጋር ተያያዥነት ያለው ጥንታዊው እና ታሪካዊው የየካ ደብረ ሳህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ሲሆን የዋሻ ሚካኤል በወቅቱ ለአካባቢውና ለአዲስ አበባ ህዝብ አገልግሎት ቢሰጥም በተለይ በቁጥር በርካታ ለሆነው ለአዲስ አበባ ህዝብ በመራቁ አጼ ምኒልክ አሁን የካ ሚካኤል ተብሎ በሚጠራው ቦታ ከእንጨት ባሰሩት መቃኞ ውስጥ የካቲት 17ቀን 1895 ዓ.ም ታቦተ ህጉን እንዳስቀመጡ የደብሩ ዋና አስተዳዳሪ መልዐከ ሣህል አባ ስዩም ወልደ ገብርኤል ለየኔ ቫይብ ዝግጅት ክፍል የገለጹ ሲሆን በንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ ከአባታቸው ሞት በኃላ በአቡነ ሳዊሮስ ቡራኬ መሰረቱን አስጀምረው አሁን የሚታየው ቤተክርስቲያን ከ1920 እስከ 1923 ዓ.ም ተሰርቶ በመጠናቀቁ የጥንታዊው የሚካኤል ውቅር ቤተክርስቲያን ፅላት ህዳር 12 ቀን 1923 ወደ አዲሱ ህንፃ እንደገባ ገልጸውልናል።

የእርግባይ ሀበሻ ትራቭል ዋና ስራ አስኪያጅ እና መስራች አቶ እርግባይ ወንድሙ በመጨረሻ ላይ ይህ ጉብኝት እንዲሳካ ጉልህ ድርሻ ለነበራቸው የከተማው ባህል ፣ ኪነጥበብ እና ቱሪዝም አመራሮች እና ሰራተኞች ፣ በጉብኝቱ ለተሳተፉ አካላት ፣ለደብረ መንክራት አቡነ ተክለሃይማኖት ወ ቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ኃላፊ ሊቀ ትጉሃን ይኸይስ ፈንቴ ፣ለየካ ደብረ ሳህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ መልዐከ ሣህል አባ ስዩም ወልደ ገብርኤል ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።

(ጌች ሐበሻ)
ፎቶ Sisay Guzay

Share Post ►

Trending Today

You may also like

Leave a Comment

* By using this form you agree you are responsible for what you comment.